🌐 Konne borro kawiinni Sidaamu Afoonni dino. Hanafu borro አማርኛnni leellishshanni no.
📄 Egenno

የጡት ካንሰር - ለማህበረሰብና ለታካሚዎች ግንዛቤ መስጫ የተዘጋጀ ጽሑፍ

📚 NCCN Hargansaanchotira Qajeelshi® Aana Ka''ino · 🌍 Itiyoophiyanna Gobbu Afirikira qixxeessamino · 👨‍⚕️ Dr. Jilcha D Feyisa

📖 የጡት ካንሰር ምንነት

ሰዉነታችን በብዙ ትሪሊየን ከሚቆጠር ህዋሳቶች የተገነባ ነዉ፡፡ ህዋሳቶች በጋራ ተሰባስበዉ ህብረህዋስ ይፈጥራሉ፡፡ እነዚህ ህብረህዋሶች ተሰብስበው በጋራ ብልቶች/የሰውነት ክፍሎችን ይፈጥራሉ። 

መራሄ (በራሂ/ Gene) በእያንዳንዱ ህዋስ ውስጥ የሚገኝ የህዋሳቶችን የመራባት ሂደት፣ እድገት፣ ስራ እና አሟሟት የሚቆጣጠር ረቂቅ ክፍል ነዉ፡፡ ማንኛዉም የህዋሳት ጠባይና የስራ ሂደት በዚህ ክፍል ዉስጥ ተመዝግቦ ይገኛል፡፡ ህዋሳት ከሚፈለገዉ በላይ እንዳይባዙ የሚከላከልም ክፍል ሲሆን መቼና እንዴት መራባት እንዳለበቸዉ ትእዛዝ የሚወጣዉ ከዚህ ክፍል ነዉ፡፡ 

መራሄ ላይ ችግር/ለዉጥ በሚፈጠርበት ሰዓት ህዋሳት በዓግባቡ መስራት ያቆማሉ፡፡ ከእነዚህ ህዋሶች የሚመነጨው ትእዛዝም ህዋሳቶች ባልተለመደ ሁኔታ እንዲሰሩ ያደርጋቸዋል። እነዚህ የተናጉ ህዋሳቶች አንዳነዴ ከቁጥጥር ዉጪ በሖነ መንገድ ይራባሉ፡፡ ይህም ብዙና ትክክለኛ ያልሆኑ ህዋሳቶች እንዲራቡ በማድረግ ካንሰር የሚባለዉ በሽታ እንዲፈጠር ምክንያት ይሆናል፡፡ ይህ የተራባው ህዋስ በጊዜ ሂደት ጤነኛ የነበሩ ህብረ ህዋሳትንም ጭምር በማጥቃት  ጤነኛውን የአካል ክፍል በሽተኛ ያደርጋል፡፡ በጊዜ ሂደትም ራቅ ብለዉ ወዳሉ ጤናማ አካላት የመበተን እድል ያገኛል፡፡ 

የጡት ካንሰር ከላይ በተብራራዉ መልኩ ከጡት ህዋሳቶች የተዛባ እና ከቁጥጥር ዉጪ በሆነ መራባት የካንሰር ባህርይ ካካበቱ እጢዎች የሚነሳ የጡት በሽታ ዓይነት ነዉ፡፡ ጡት በተፈጥሮ በውስጡ ወተት ለማመንጨት የሚያስችሉ በርካታ ከረጢት መሰል ነገሮች አሉት፡፡ እነዚህን ነገሮች ከጡት ጫፍ ጋር የሚያገናኙ ቱቦዎች ያሉት ሲሆን እነዚህ ቱቦዎች በእርግዝና ወቅት ወተት ለማመንጨት ትልቅ ሚናን ይጫወታሉ፡፡ የጡት ካንሰር በአብዛኛው ማደግ የሚጀምረው በእነዚህ ቱቦዎች ውስጥ ነው፡፡ ከተቀሩት የጡት ክፍሎችም  የመነሳት እድሉ ሰፊ ነዉ፡፡  

📖 የጡት ካንሰር በኢትዮጵያ

በዓለማችን ላይ በየዓመቱ ከ1ሚሊዮን በላይ ግለሰቦች በጡት ካንሰር ይያዛሉ፡፡ የጡት ካንሰር በኢትዮጵያ ከጊዜ ወደጊዜ አሳሳቢ በሆነ ደረጃ እየጨመረ ነዉ፡፡ የጡት ካንሰር በኢትዮጵያ በሴቶች ላይ ከሚከሰቱ ከሁሉም የካንሰር ዓይነቶች ቀዳሚዉ ነዉ፡፡ በካንሰር በሺታ ተይዘዉ ወደ ጥቁር አንበሳ ሆስፒታል ከሚመጡ የአዲስ አበባ ኗሪዎች መካከል 32.8% ታካሚዎች የጡት ካንሰር የተያዙ ናቸዉ፡፡ በኢትዮጵያ ከ40 እስከ 65 ያለዉ እድሜ በዋናነት የጡት ካንሰር የሚከሰትበት እድሜ ሲሆን ከሃያዎቹ ጀምሮ ባለ ማንኛዉም የእድሜ ክልል ዉስጥ ያሉ ሴቶች ላይ በብዛት እየተስተዋለ ነዉ፡፡   

📖 ለጡት ካንሰር ተጋላጭነት

ማንኛዉም ሰዉ በጡት ካንሰር የመጠቃት እድል አለዉ፡፡ አብዛኛዉን ጊዜ በሴቶች ላይ የሚከሰት በሽታ ሲሆን አልፎ አልፎ በወንዶችም ላይ ይከሰታል፡፡ የጡት ካንሰር በሽታ መንስኤዎች ለጊዜው ባይታወቁም ማግባት፣ አለማግባት፣ መዉለድ አለመዉለድ በበሽታዉ ላለመያዝ ዋስትናዎች አይደሉም፡፡ ለጡት ካንሰር ተጋላጭ የሚያደርጉ ነገሮች በርካታ ሲሆኑ ጥቂቶቹ እንደሚከተለዉ ተብራርተዋል፡-

  1. እድሜ፡ የእድሜ መጨመር እንደሌሎቹ የካንሰር ዓይነቶች ለጡት ካንሰር መከሰት ዋነኛዉ ምክንያት ነዉ፡፡ በአብዛኛዉ ከ50 ዓመት በላይ ያሉ ሴቶች የመጠቃት እድላቸዉ በከፍተኛ ሁኔታ እየጨመረ ይሔዳል፡፡ ሆኖም ከአስራቤቶቹ እድሜዎች ጀምሮ በማንኛዉም የእድሜ ክልል ላይ ሊከሰት ይችላል፡፡ 

  2. የሆርሞኖች መዛባት፡ የጡት ካንሰር በሴቶች ዉስጥ ከሚመነጭ ኤስትሮጂን የሚባል ሆርሞን ተጋላጭነት በጨመረ ቁጥር የመከሰት እድሉም እየጨመረ ይሔዳል፡፡ የወር አበባቸዉ ከአማካይ እድሜ ቀደም ብሎ የሚመጣባቸዉ ወይም ዘግይቶ የሚቆምባቸዉ ሴቶች፣ ልጅ ያልወለዱ ሴቶች፣ በጊዜ የማይወልዱ (የመጀመሪያ እርግዝናቸዉ ከ30 ዓመት በኋሏ ሲሆን) አሊያም ጥቂት ልጆች ብቻ ያረገዙ ሴቶች፣ ለረጅም ዓመታት የወሊድ መቆጣጠሪያ እንክብሎችን  የሚጠቀሙ ሴቶች አሊያም በመድኃኒትነት የጠዘጋጀ ሆርሞን የሚወስዱ ሴቶች፣ ጡት ያላጠቡ ሴቶች ለጡት ካንሰር ተጋላጭነታቸዉ ይጨምራል፡፡ ከመጠን ያለፈ ዉፍረት ከዚሁ ምክንት ጋር ሊያያዝ በሚችል መልኩ ተጋላጭነትን ይጨምራል፡፡ 

  3. ጤናማ ያልሆነ አመጋገብ፡ ቅባትነትንና ጣፋጭነትን ያላቸዉ ምግቦች አዘዉትሮ መመገብ እንዲሁም አልኮል አዘዉትሮ መጠጣት ተጋላጭነትን ይጨምራል፡፡ በቂ ቫይታሚን አለማግኘትም በካንሰር የመያዝ እድልን ይጨምራል፡፡

  4. የመራሄ ለዉጥ/ የዘር ዉርስ፡ የጡት ካንሰር ሊያመጡ የሚችሉ በርካታ የመራሄ ለዉጦች (genetic mutations) የተለዩ BRCA-1 እና BRCA-2 በመባል የሚታወቁት ዋንኞቹ ናቸዉ፡፡ የእነዚህ መራሄ ለዉጥ ያለበት ሰዉ በጡት ካንሰር የመያዝይጨምምል፡፡ በቤተሰብ ዉስጥ ቀድሞ ተከስቶ የሚየዉቅ የጡት ካንሰር ለዚህ አንድ ምልክት ሊሆን ይችላል፡፡ በእንደዚህ ዓይነት ቤተሰብ ዉስጥ ያሉና በደም የሚዛመዱ ሰዎች በጡት ካንሰር የመያዝ እድላቸዉ ይጨምራል፡፡ 

  5. ከዚህ በፊት በጡት ካንሰር ተጠቅቶ የሚያዉቅ ዳግም በጡት ካንሰር የመያዝ እድሉ ከፍ ያለ ነዉ፡፡ 

  6. ከ30 ዓመት በፊት ለጨረር ተጋላጭ የሆኑ ሰዎች፡ ይሀ በጨረሩ ዓይነትና መጠን የሚወሰን ነዉ፡፡

  7. ሲጋራ ማጨስ 

  8. የአኗኗር ዘዬ ና የመኖሪያ ሰፍራ፡ የምእራባዊያን የኑሮ ዘዬ ለጡት ካንሰር ተጋላጭነትን ይጨምራል፡፡ ከገጠር ይልቅ በከተማ የሚኖረ ሴቶች የበለጥ ተጋላጭ ናቸዉ፡፡ 

📖 የጡት ካንሰር ምልክቶች

እብጠት፣ የጡት ቆዳ ከለር መቀየር፣ የጡት ጫፍ መሰርጎድ ወይም ወደዉስጥ መገልበጥ፣ ቁስለት፣ ከጡት ጫፍ አሊያም በቆሰለዉ  ቦታ የሚወጣ ፈሳሽ፣ የሁለቱ ጡት መጠንና ቅርጽ መለያየት እና በብብት ስር የሚታዩ ትናንሽ እባጮች አዘዉትረዉ የሚታዩ የጡት ካንሰር ምልክቶች ናቸዉ፡፡ የጡት ጫፍ ማሳከክ፣ የሚቀረፍ ቁስል ወይም ሽፍታ፣ የጡት ጫፍ ወይም ሌላ የጡት ክፍል መዝቀጥ፣ ባልታሰበ ጊዜ በጡት ጫፍ የሚታይ ፈሳሽ፣ ከአንድ ቦታ ላይ የሚሰማ የማይለቅ አዲስ ሕመም ሌሎች የጡት ካንሰረን የሚጠቁሙ ምልክቶች ናቸዉ፡፡ 

እብጠት ዋንኛዉ የጡት ካንሰር  ምልክት ሲሆን አብዛኛዉን ጊዜ ህመም የለዉም፡፡ ቁስለት እየፈጠረ ሲሄድ አሊያም ደረጃዉ እየጨመረ ሲሄድ ግን የህመም  ስሜት እየፈጠረ ይሄዳል፡፡  ሁሉም የጡት እባጮች የጡት ካንሰር ላይሆኑ ይችላሉ፡፡ ሆኖም ካንሰር የመሆን ሰፊ እድልም ሰለሚኖር  እባጭ  እንደተስተዋል ፈጥኖ ሃኪምን ማማከር ያስፈልጋል፡፡ የጡት ካንሰር ወደ ሳምባ፣ ጉበት፣ የጀርባ አጥምት፣ የራስቅል እና ሌሎች የሰዉነት ክፍሎች የመበተን ጠባይ ያለዉ ስለሆነ ወደነዚህ ቦታዎች መበተኑን ተከትሎ ሳል፣ የሆሆና የጀርባ ህመም፣ ራስ ምታት፣ የሰዉነት ክብደት መቀነስ፣ የምግብ ፍላጎት ማጣት፣ መደካከም እና የመሳሰሉ ምልክቶች ሊከሰቱ ይችላሉ፡፡

📖 የጡት ካንሰር ቅድመ ምርመራ

የጡት ካንሰር ቅድመ ምርመራ የካንሰር ደረጃ ከፍ ሳይል በጊዜ ለመለየትና ለማከም ያስችላል፡፡ ይህ የሚደረገዉ ምልክቶች መታየት ከመጀመራቸዉ በፊት ነዉ፡፡ የጡት ካንሰርን በጊዜ መለየት የሚያስችሉ በርካታ መንገዶች አሉ፡፡ እነዚህም፡-

  1. በቤተሰብ ያለ ታሪክ ካለ መለየት፡ ከላይ እንደተጠቀሰዉ የጡት ካንሰር በቤተሰብ ሊተላለፍ የሚችል በሽታ ነዉ፡፡ ስለዚህም በቤተሰብ ዉስጥ በጡት ካንሰር ተይዞ ወይም ህይወቱ አልፎ የሚያዉቅ ካለ ጠይቆ መረዳት ሊኖር ስለሚችለዉ ስጋት ጠቋሚ ነዉ፡፡ ስለ ቤተሰብ የጤና ታሪክ ከታወቀ በኋላም ወደ ሃኪም በመሄድ ሊደረግ ስለሚገባዉ ክትትልና ምርመራ ማወቅ ተገቢ ነዉ፡፡


  1. በራስ ላይ የሚደረግ የጡት ምርመራ/ፍተሻ ማድረግ፡ የራስን ጡት በየጊዜዉ መዳሰስ የጡት ካንሰርን በጊዜ ለመለየትና ለመከላከል ያስችላል፡፡ ምንጊዜም ገላን ለመታጠብ ወደሻወር ቤት በሚገባበት ጊዜ፣ ጊዜ ወስዶ ጡትን ማየት ተገቢ ነዉ፡፡ ቀጥሎ ያለዉ ምስል  የራስን ጡት እንዴት እንደሚዳሰስ የሚያሳይ ሲሆን ሲዳስሱ ቀጥሎ የተመለከቱት ስለመኖራቸዉ ማስተዋል ይገባል፡ የተለየ መጓጎል ወይም መጎርበጥ፣ በጡት ዉስጥ ወይም በብብት ስር ያለ መጠጠር ወይም ዉፍረት፣ እብጠት፣ የሙቀት ስሜት፣ ከጡት ላይ ያለ ቀይ ወይም ጥቁር ምልክት፣ የጡት መጠን ወይም ቅርጽ ለውጥ እና የቆዳ መጥለቅ ወይም መሸብሸብ፡፡ በጡት ላይ የሚደረግ የግል ፍተሻ ቢያንስ በየወሩ ሊካሄድ ይባዋል፡፡




    1. በራስ ላይ ሚደረግ የጡት ፍተሻ/ምርመራ የመጀመሪያዉ ደረጃ ከወገብ በላይ እራቁት በመሆን መስታወት ፊት ለፊት በመቆም የሚደረግ ነው። እጅዎን በወገብዎ ላይ በማድረግ የተለመደውን የጡትዎን ቅርጽ ማጥናት፡፡ በተመሳሳይ መልኩ እጅን በራስ ላይ በማድረግ የጡቶችን ቅርጽ ማጥናት። ከመሰታወት ፊት ለፊት የተለመደውን የጡት ቅርጽ ጠንቅቆ ማወቅ በጊዜ ብዛት ወይንም በሌሎች የጤና እክሎች ምክንያት ሊመጡ የሚችሉ ለውጦችን ለይቶ ለማወቅ ይረዳል።

    1. ሊፈትሹ ባሰቡት ጡትዎ በኩል ያለውን እጅዎን ከራስዎ በላይ በመዘርጋት በሌላኛው እጅዎ ሶስት ጣቶችዎን በመጠቀም በክብ በማንቀሳቀስ ከብብት ስር ጀምሮ ጡትዎን በሙሉ በሚገባ መፈተሽ። ፍተሻዎ እጅዎ በሚንቀሳቀስበት ወቅት በጡትዎ ውስጥ ያበጠ ወይም የጠጠረ ነገር መኖርና አለመኖርዋን ለማረጋገጥ ነው። ያበጠ ወይም የጠጠረ ነገር ካገኙ ደጋግመው በመፈተሽ ማረጋገጥ ይገባል፡፡ የጡትዎን ጫፍ በመጫን ከጡትዎ ውስጥ የሚወጣ ፈሳሽ መኖር አለመኖሩን መፈተሽ ይገባል። ጡት የማያጠቡ ከሆነና ፈሳሽ የሚወጣዎት ከሆነ ማረጋገጥ ይገባል፡፡ እነዚህ ምልከቶችን ካዩ ወዲያዉ ወደ ሀኪም መሄድ ያስፈልጋል፡፡ 

    1. በጀርባ በመንጋለልና ሊፈትሹ ባሰቡት ጡትዎ በኩል ያለውን እጅዎን ከራስዎ በላይ በመዘርጋት በሌላኛው እጅዎ ሶስት ጣቶችዎን በመጠቀም በክብ በማንቀሳቀስ ከብብት ስር ጀምሮ ጡትዎን በሚገባ መፈተሽ። ፍተሻዎ እጅዎ በሚንቀሳቀስበት ወቅት በጡትዎ ውስጥ ያበጠ ወይም የጠጠረ ነገር መኖርና አለመኖርዋን ለማረጋገጥ ነው። ያበጠ ወይም የጠጠረ ነገር ካገኙ ደጋግመው በመፈተሽ ማረጋገጥ ይገባል፡፡ 

    1. የጡት ሶኖግራፊ፡ ሶኖግራፊ (አልትራሳዉንድ) በጡት ላይ ያሉ እባጮችን በቀላሉ መመልከት የሚያስችል የምርመራ ዓይነት ነዉ፡፡ ከጨረር ነጻ የሆነ ስለሆነ የጡት እባጭ ስለመኖሩ ቅድመ ካንሰር ምርመራ ለማድረግ ተመራጭ ያደርገዋል፡፡ 


    1. የጡት ማሞግራፊ፡ ማሞግራፊ አነስተኛ ጨረር በመጠቀም የሚደረግ የጡት ምርመራ ነው። የማሞግራፊ ምስሎች ዝርዝር ያለ ምስል እና ጡቶችን ከተለያየ አቅጣጫ የሚያሳይ ነው። ጡት በሁለት ከፕላስቲክ በተሰሩ ጠፍጣፋ ትሪዎች መካከል ይደረጋሉ። እነዚህ ትሪዎችን በመጫን ጡትንም ጠፍጣፋ እንዲሆን ይደረጋል። በጣም አነስተኛ ጨረርን በመጠቀም ጡትን በመጫን ጥራት ያለው ምስል ለማግኘት ይረዳል።


    1. የጡት ኤም አር አይ (MRI)፡ ማግኔትንና ኮምፒተርን በመጠቀም የውስጥ ሰውነትን አጣርቶ የሚያሳይ መሳሪያ ነው፡፡ ጥቃቅን የሐሖነ እብጠቶችን ና ዉጦችን ለይጦ የማየጥ አቅም ስላለዉ ለጡት በቅድመ ካንሰር ምርመራነት ያገለግላል፡፡

📖 የጡት ካንሰርን በህክመና ማረጋገጥ

በቅድመ ካንሰር ምርመራ ጊዜ የሚያጠራጥር ወይም ጠቋሚ ምልክቶች ከታዩ አሊያም የጡት ላይ ምልከቶች ያለቅድመ ካንሰር ምርመራ ከታዩ ካንሰር ሥለመሆን አለመሆኑ በተለያዩ የምርመራ ዘዴዎች ማረጋገጥ ይቻላል፡፡ እነዚህ የምርመራ አይነቶች ቀጥለዉ የተብራሩ ናቸዉ ፡-

  1. FNAC፡ በመርፌ እባጭ ካለበት ቦታ ናሙና በመዉሰድ በስነደዌ ስፔሻሊስት ሀኪሞች የእጢነት ጠባይ ያላቸዉ ህዋሳቶች መኖር አለመኖራቸዉን የሚላይ ዘዴ ነዉ፡፡

  1. BIOPSY፡እንደ FNAC ናሙና በመዉሰድ በስነደዌ ስፔሻሊስት ሀኪሞች የእጢነት ጠባይ ያላቸዉ ህዋሳቶች መኖር አለመኖራቸዉን የሚላይ ዘዴ ሲሆን በዚህ መንገድ በመርፌ ሣይሆን ዕጢዉን እንዳለ በማዉጣት አሊያም ብዛት ያለዉ የናመነና መጠን ቆርጦ በመዉሰድ የሚደረግ ምርመራ ነዉ፡፡ ብዙዉን ጊዜ የማረጋገጫ ዉጠየት የሚሰጥ ነዉ፡፡ 

  1. የደም ምርመራ ፡ በሽታዉ ያስከተለዉን ጉዳቶች ለመለየት እና ለመከታተል ይረደል፡፡ 

  1. የኤክሰሬይ ና ሶኖግራፊ ምርመራ፡ ወደ ሳመባ፣ ወደ ጉበትና የመሳሰሉ የሰዉነት ክፍሎች የተሰራጨ በሽታ ካለ ለመለየት ይጠቅማሉ፡፡ እነዚህ የምርመራ ዓይነቶች ከመጀመሪያዉ ጀምሮ ለሁሉም ታካሚዎች የሚደረጉ ምርመራዎች ናቸዉ፡፡ በክትትል ሰዓትም የህክምናዉን ዉጤት ለማየትና አዲስ የተመለሰ/የተስፋፋ በሸታ መኖር አለመኖሩን ለመከታተል ይረዳሉ፡፡  

  1. የጡት ሲቲ ስካን (CT)  እና የጡት ኤም አር አይ (MRI)፡ እነዚህ እንደአስፈላጊነቱ ወደሌላ የሰወነት ክፍል የተሰራጨ በሽታ መኖር አለመኖሩን ለመለየት የሚረዱ መሳሪያዎች ናቸዉ፡፡ 

📖 የጡት ካንሰር ህክምና

የጡት ካንሰር በጊዜ ከታወቀና ከታከመ ሙሉ በሙሉ ሊድን የሚችል በሽታ ነዉ፡፡  በጊዜ መታከም ካልቻለና ወደሌላዉ የሰዉነት ክፍል ከተሰራጨ ወደሞት ሊያደርስ የሚችል በሽታ ነዉ፡፡ ለጡት ካንሰር ህመም የሚደረግ ህክምና በእብጠቱ ዓይነት፣ በእብጠቱ መጠን፣ በመዛመት ባህርይውና በህመምተኛው ሁኔታ የሚወሰን ነዉ፡፡ በአብዛኛዉን ጊዜ የጡት ካንሰር ህክምና ሙሉበሙሉ ለመፈወስ በማሰብ የሚደረግ ጥረት ነዉ፡፡በየትኛዉም ደረጃ ቢሆን የጡት ካንሰርን ማከም ቢያንስ የካንሰሩን መጠን በመቀነስ ወይም እድገቱን በመገደብ  እድሜን ማርዘም እንዲሁም አኗኗር ከስቃይ ነጻ እንዲሆን ማድረግ ያስችላል፡፡ 

የጡት ካንሰር መኖሩ ከተረጋገጠ በኋላ በተለያዩ መንገዶች ህክምና ይደረጋል፡፡ ከእነዚህ መንገዶች መካከልም የቀዶ ህክምና፣ የጨረር ህክምናና የመድኃኒት ህክምና (ኬሞቴራፒ፣ የሆርሞን ህክምና  እና የታርጌትድ ቴራፒ ህክምና) ዋንኞቹ ናቸው፡፡   በአብዛኛዉ ሁላት ወይም ከዚያ በላይ የህክምና ዓይነቶችን በመጠቀም ይታከማል (ለምሳሌ የቀዶ ህክምና ከዚያም የኬሞቴራፒ ህክምና፣ የሆርሞናል ህክምና እና የጨረር ህክምናን በማስቀጠል ይታከማል)፡፡ 

  1. የቀዶ ጥገና ህክምና፡ የቀዶ ጥገና ህክምና እብጠቱ የተከሰተባቸውን የሰውነት ክፍሎች በቀዶ ጥገና ቀዶ የማውጣት ሕክምና ነዉ፡፡ በቀዶ ህክምና ጡት ሊቆረጥ የሚችለዉ በሽታዉ ወደ ሌላ ቦታ ያልተዛመተ ከሆነ ብቻ ነዉ፡፡ ስለዚህም በቀዶ ህክምና መታከም መቻል ለጡት ካንሰር ህክምና በጊዜ መድረስ መቻልን ያመላክታል፡፡ ጡትን በቀዶ ህክምና ቆርጦ ማዉጣት በሰውነት ቅርፅ ላይ ለውጥ የሚያስከትል በመሆኑ በብዙ ታማሚዎች ዘንድ የማይመርጥ ህክምና ነው፡፡ በእነደዚህ ዓይነቱ ሃሳብ ዉስጥ ታካሚዎች ጊዜ ስለሚያጠፉ የጡት ካንሰር መታከም የሚችልበት ወርቃማ ጊዜ ይባክናል፡፡ ወደ ሌላ አካላትም ይሰራጫል፡፡ በዚህ ደረጃ ደርሶ በቀዶ ህክምና ሙሉ በሙሉ ለማዳን ማሰብ ከባድ ነዉ፡፡ የህክምናዉ ዓላማም ሙሉበሙሉ ማዳን ከሚለዉ እድሜን ማራዘም ወደ ሚል ዓላማ ይወርዳል፡፡ ስለዚህም ያልተሰራጨን የጡት ካንሰር ለማዳን ቀዶ ህክና በጣም አስፈላጊ የሆነ የህክምና ክፍል ስለሆነ ገዜ ባለማባከን ታካሚዎች ሃሳቡን ተቀብለዉ ቀዶህክምናዉ እንዲያደርጉ ይመከራል፡፡ ከትዳር ጋር ተያይዞ ያሉ የሥነልቦና ጫናዎችም ሴቶች በጊዝ መወሰን እንዳይችሉ ስለሚያደርግ የትዳር አጋሮችና መላዉ ቤተሰብ ታካሚዉ ፈጥኖ ዉሳኔ ላይ እንዲደርስ በሓሳብ እገዛ ማድረግ ይኖርባቸወል፡፡ 


ከቀዶ ህክምና በኋላ እጅ ተቆርጦ የወጣበት ቦታ ላይ ተመለሶ የማበጥ ምልክት ሊታይ ይችላል፡፡ ስለዚህም ተቆርጦ የወጣበት ቆዳ ላይ፣ ጤናማዉ ጡት ላይ፣ ሁለቱም ብብት ስር እንዲሁም አንገት ላይ (ከብራኳ/clavicle) አጥንት በላይ ጥቃቅን እባጮችን ጭምር በየጊዜዉ ማየት ያስፈልጋል፡፡ ከተገኙም በአፋጣኝ ክትትሉን እየደረገ ላለ ሃኪም መናገር ያስፈልጋል፡፡  ወደካንሰርነት የተቀየሩ ህዋሳቶች ወደደም ዝዉዉር ስለሚገቡ ከቀዶ ህክምናዉ በኋላ ወደ ጉበት ሳምባ የጀርባ አጥንት የራስ ቅል አሊያም ሌሎቸ ቦታዎች ላይ ሊሰራጭ ይችላል፡፡ አነዚህ በቦታዉ ላይ ደግሞ የሚነሱ ወይም ከቀዶ ህክምና በኋላ ተሰራጭተዉ የሚመጡ በተለያ ህክምና ሰለሚደረግላቸዉ ፈጥነዉ ማማከር ይኖርባቸዋል፡፡  ከቀዶ ህክምና በኋላ እጅ የማበጥ ምልክት ሊያጋጥም ይችላል፡፡ ይህም የሚሆነዉ ካንሰር ሊሰራጭ የሚችልባቸዉ መንገዶች በቀዶ ህክምናዉ ተቆርጠዉ ስለሚወጡ ነዉ፡፡ 


  1. የጨረር ህክምና፡ ካንሰሩ ያለበት አካባቢን ከፍተኛ ሃይል ያለዉ የጨረር ኃይል በማስመታት የሚደረግ ህክምና ነዉ፡፡ ለጡት ካንሰር ከቀዶ ህክምና በኋላ የቀሩ ወደካንሰርነት የተለወጡ ህዋሳቶችን ለማጥፋት ይሰጣል፡፡ ይህም ካንሰሩ ደግሞ እንዳይነሳ ያደርጋል፡፡ የጨረር ህክምና አጭር ጊዜ የሚፈጅና በሚሰጥበት ጊዜም ምንም ዓይነት ህመም የማይፈጥር የህክምና ዘዴ ነዉ፡፡ መጠነኛ የሖኑ የጎንዮሽ ጉዳቶች ሊያጋጥም ይችላል፡፡


  1. የመድሃኒት ህክምና (ኬሞቴራፒ፣ የሆርሞን ህክምና  እና የታርጌትድ ቴራፒ ህክምና)፡ የመድኃኒት ህክምና የጡት ካንሰርን ለማከም በሰፋት ከሚዉሉ የህክምና ዘዴዎች አንዱ ነዉ፡፡ ኬሞቴራፒ፣ የሆርሞን ህክምና  እና የታርጌትድ ቴራፒ የመድኃኒት ህክምና ስር የሚካተቱ ናቸዉ፡፡ ህክምና የጐንዮሽ ጉዳቶች አሉት - ማቅለሽለሽ፣ ማስመለስ፣ የፀጉር መርገፍ፣ መድማት፣ የልብ ህመም፣ የወር አበባ መቅረት፣ መካንነት በሽታን የመከላከል አቅምን ማዳከም ዓይነት የጎንዮሽ ጉዳቶች አሉት፡፡ ህክምናዉ ካለቀ በኋላም በጡት ካንሰር በሽታ የተያዙ ሰዎች ዘላቂና ቢያንስ ለ10 ዓመታት የሚዘልቅ የጡት ካንሰር ህክምና ክትትል ያስፈልጋቸዋል፡፡


  1. ኬሞቴራፒ፡ የካንሰር ህዋሳቶችን መግደል ወይም እንዳይራቡ ማድረግ የሚችሉ መድኃኒቶች በመስጠት የሚደረግ ህክምና ነዉ፡፡ በአብዛኛዉ የቀዶ ህክምና ከተደረገ በኋላ የሚሰጥ ህክምና ሲሆን አልፎ አልፎ ከቀዶ ህክምና በፊት ሊሰጥ ይችላል፡፡ የጊዜዉ መቼታ እንደአጢዉ ዓይነት የሚወሰን ይሆናል፡፡ የተሰራጨ የጡት ካንሰር በቀዶ ህክምና ስለማይታከም በዋናነት የሚታከመዉ በኬሞተራፒ ነዉ፡፡ ከ 4 እስከ 8 ዙር የሚሰጥ ሲሆን አልፎአልፎ ሊያንስ ወይም ሊበልጥ ይችላል፡፡ ቤ3 ሣምንት፣ በሻምንቱ አሊያም ከዚያ ዉጪ በሆን ጊዜ ይሰጣሉ፡፡ የመድኃኒቱ ዓይነትም የእጢዉን ለዉጥ በማየት ሊቀየር ይችላል፡፡


  1.  የሆርሞን ህክምና፡ አንዳንድ የጡት ካንሰር ከመነሻዉ ጀምሮ ኤስትሮጂን እና ፕሮጄስትሮጂን በሚባሉ ሆርሞኖች አማካይነት ሊነሳ ወይም ከተነሳ በኋላ ሊጠናከር ይችላል፡፡ እነዚህን ሆርሞኖች እንዳይመነጩ አሊያም እንዳይሰሩ የሚያደርጉ መድኃኒቶች የጡት ካንሰርን ለማከም ይረዳሉ፡፡ እነዚህ መድኃኒቶች  የሆርሞን ሪሰፕተር ፖሰቲቭ በሆኑ ታካሚዎች ላይ ዉጤታማ ናቸዉ፡፡ በአብዛኛዉ ለ5ዓመታት ያለመቋረጥ የሚሰጡ መድኃኒቶች ናቸዉ፡፡ ታሞክሲፈን፣ አናስትራዞል ና ሌትሮዘል በእኛ ሃገር በብዛት የምንጠቀምባቸዉ መድኃኒቶች ናቸዉ፡፡


  1. ታርጌትድ ቴራፒ፡ እነዚህ ለእጢ መነሳት ምክንያት የሆኑ መራሄዎች ላይ ወይም የመራሄ መገለጫ የሆኑ ፐሮቲኖች ላይ የሚሰሩ መድኃኒቶች ናቸዉ፡፡ በስፋት ለጡት ህክምና እየዋሉ ያሉ ሲሆኑ ዋጋቸዉ ከፍተኛ በመሆኑ በእኛ ሃገር አይገኙም፡፡

📖 የጡት ካንሰር ህክምና ዉጤት

የጡት ካንሰር ህክምና ከጊዜ ወደጊዘዜ እየተሻሻለ በመሄዱ ከህክምናዉ በኋላ የሚሞቱ ሰዎች ቁጥር እየቀነሰ ነዉ፡፡ የጡት ካንሰር ህክምና ዉጤት ሙሉ በሙሉ መፈወስ፣ የእብጠቱ መጠን መቀነስ አሊየያም በነበረበት ሳይጨምር እንዲቀጥል ማድረግ ሊሆን ይችላል፡፡ ይህም እንደደረጃዉና እንደህክምና ዓይነቱ ሊለያይ ይችላል፡፡ በመጀመሪያዎቹ ደረጃ ላይ ያለ ካንሰር የመዳን ዕድሉ ሰፊ ስለሆነ የጡት ካንሰር ያለበት ማንኛዉም ሰዉ በጊዜ ህክምናዉን መጀመር ይኖርበታል፡፡
⚕️
የሕክምና ማሳሰቢያ

ይህ ይዘት ለትምህርታዊ ዓላማዎች ብቻ ሲሆን፣ በ NCCN መመሪያዎች እና የዓለም ጤና ድርጅት (WHO) ምክሮች ላይ የተመሠረተ ነው። ከብቁ የጤና ባለሙያ የሚሰጥ ምክርን አይተካም። የኢትዮጵያ ሕሙማን፦ እባክዎ የጥቁር አንበሳ ስፔሻላይዝድ ሆስፒታል ኦንኮሎጂ ክፍልን ያማክሩ።