ሰዉነታችን በብዙ ትሪሊየን ከሚቆጠር ህዋሳቶች የተገነባ ነዉ፡፡ ህዋሳቶች በጋራ ተሰባስበዉ ህብረህዋስ ይፈጥራሉ፡፡ እነዚህ ህብረህዋሶች ተሰብስበው በጋራ ብልቶች/የሰውነት ክፍሎችን ይፈጥራሉ።
መራሄ (በራሂ/ Gene) በእያንዳንዱ ህዋስ ውስጥ የሚገኝ የህዋሳቶችን የመራባት ሂደት፣ እድገት፣ ስራ እና አሟሟት የሚቆጣጠር ረቂቅ ክፍል ነዉ፡፡ ማንኛዉም የህዋሳት ጠባይና የስራ ሂደት በዚህ ክፍል ዉስጥ ተመዝግቦ ይገኛል፡፡ ህዋሳት ከሚፈለገዉ በላይ እንዳይባዙ የሚከላከልም ክፍል ሲሆን መቼና እንዴት መራባት እንዳለበቸዉ ትእዛዝ የሚወጣዉ ከዚህ ክፍል ነዉ፡፡
መራሄ ላይ ችግር/ለዉጥ በሚፈጠርበት ሰዓት ህዋሳት በዓግባቡ መስራት ያቆማሉ፡፡ ከእነዚህ ህዋሶች የሚመነጨው ትእዛዝም ህዋሳቶች ባልተለመደ ሁኔታ እንዲሰሩ ያደርጋቸዋል። እነዚህ የተናጉ ህዋሳቶች አንዳነዴ ከቁጥጥር ዉጪ በሖነ መንገድ ይራባሉ፡፡ ይህም ብዙና ትክክለኛ ያልሆኑ ህዋሳቶች እንዲራቡ በማድረግ ካንሰር የሚባለዉ በሽታ እንዲፈጠር ምክንያት ይሆናል፡፡ ይህ የተራባው ህዋስ በጊዜ ሂደት ጤነኛ የነበሩ ህብረ ህዋሳትንም ጭምር በማጥቃት ጤነኛውን የአካል ክፍል በሽተኛ ያደርጋል፡፡ በጊዜ ሂደትም ራቅ ብለዉ ወዳሉ ጤናማ አካላት የመበተን እድል ያገኛል፡፡
የጡት ካንሰር ከላይ በተብራራዉ መልኩ ከጡት ህዋሳቶች የተዛባ እና ከቁጥጥር ዉጪ በሆነ መራባት የካንሰር ባህርይ ካካበቱ እጢዎች የሚነሳ የጡት በሽታ ዓይነት ነዉ፡፡ ጡት በተፈጥሮ በውስጡ ወተት ለማመንጨት የሚያስችሉ በርካታ ከረጢት መሰል ነገሮች አሉት፡፡ እነዚህን ነገሮች ከጡት ጫፍ ጋር የሚያገናኙ ቱቦዎች ያሉት ሲሆን እነዚህ ቱቦዎች በእርግዝና ወቅት ወተት ለማመንጨት ትልቅ ሚናን ይጫወታሉ፡፡ የጡት ካንሰር በአብዛኛው ማደግ የሚጀምረው በእነዚህ ቱቦዎች ውስጥ ነው፡፡ ከተቀሩት የጡት ክፍሎችም የመነሳት እድሉ ሰፊ ነዉ፡፡